በፓኪስታን የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የሕግ ባለሙያ የሆኑ ጥንዶች የ10 ዓመት እስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፓኪስታን የፀረ-ሽብር ፍርድ ቤት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እና የሕግ ባለሙያ በሆኑ ባል እና ሚስት ላይ የ10 ዓመት እስር ፈረደባቸው።
ኢማን ማዛሪ እና በባለቤቷ ሀዲ አሊ ቻታ ላይ ይህ ውሳኔ የተላለፈው ባለው ዓመት የእንግሊዝ ክሪኬት ስፖርት ቡድን በፓኪስታን ጉብኝት እያደረገ ባለበት ወቅት ፈጽመዋል በተባለ የፀጥታ ማደፍረስ ክስ ጥፋተኛ በመባላቸው ነው።
በወቅቱ ጥንዶቹ በእስላማባድ የመንገድ ማገጃዎችን በማንሳት የፖሊስ መኮንኖችን ስራ አስተጓጉለዋል በሚል ተከሰዋል። ጥንዶቹ ግን ይህን ክስ አስተባብለዋል።
ማዛሪ እና ቻታ ከዚህ ቀደም የአገሪቱን የፀጥታ ኃይል የሚተቹ ጽሁፎች በማህበራዊ ሚዲያ አሰራጭተዋል በሚል 17 ዓመት የሚደርስ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር።
ሆኖም የፓኪስታን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በነሐሴ ወር እነዚህን የቅጣት ውሳኔዎች አግዶ የነበረ ቢሆንም፣ ጥንዶቹ ከመፈታታቸው በፊት ፖሊስ በድጋሚ አስሯቸዋል። ላለፉት በርካታ ወራትም በራዋልፒንዲ በሚገኘው አዲያላ ማረሚያ ቤት ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።
ቻታ ለ“ዶውን ኒውስ” በሰጠው አስተያየት "እየተቀጣሁ ያለሁት የሚስቴን ሥራ እና የመብት ተሟጋችነት በመደገፌ ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ኢ-ፍትሃዊነትን የመቃወም ተግባር የጋራ የህይወት ጉዞ አድርገን በመምረጣችንም ጭምር ነው” በማለት ተናግሯል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥንዶቹ ግልጽ እና ፍትሃዊ የሆነ የፍርድ ሂደት እንደተነፈጋቸው ገልጿል።




















